ጥቅምት፣ 22/ 2013 . በኦሮሚያ ክልል፣ በምዕራብ ወለጋ ዞን፣ ጉሊሶ ወረዳ ማንነትን መሰረት ያደረገ ነው በተባለው ጥቃት በርካቶች መገደላቸውን ተከትሎ መንግሥት ችግሮቹን ለመፍታት እየሄደበት ያለው መንገድህጋዊ ነውብሎ እንደማያምን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ አስታውቋል።

ጎጎላ ቃንቃ በተባለው ቀበሌ በደረሰው ጥቃት የኦሮሚያ ፖሊስ 32 ሰዎች መገደላቸውን ሲገልፅ አምነስቲ የአይን እማኞችን አባሪ አድርጎ የሟቾችን ቁጥር 54 አድርሶታል።

ኢሰመጉ በዛሬው ዕለት፣ ጥቅምት 24/ 2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ “መንግሥት አሁን ላይ ችግሮቹን ለመፍታት እየሄደበት ያለው መንገድ ሕጋዊ፣ ትክክለኛ እና ተገቢ ነው ብሎ አያምንም። “ብሏል።

መንግሥት ጥቃቱን በማድረስ እና በመደገፍ የሚጠረጥራቸውንና የሚወነጅላቸውን አካላት ለፍርድ ማቅረብ ይገባዋል ይላል- የኢሰመጉ መግለጫ

“የሚወነጅላቸውን አካላት በመግለጫዎች ከማውገዝ ባለፈ፣ በሕግ የተሰጠውን ስልጣን ተጠቅሞ አጥፊዎችን ለፍርድ እንዲያቀርብ እና ለተጎጂዎች ፍትሕ እንዲሰጥ ዳግም ይጠይቃል። በማለትም አስፍሯል።

ከዚህም በተጨማሪ በጥቃቱ የቆሰሉ ሰዎች አፋጣኝ ህክምና እንዲያገኙ፣ በስጋት መኖሪያቸውን ለቅቀው የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ እንዲያደርግ የጠየቀው መግለጫው በተጨማሪም ንብረታቸው ለወደመባቸው ተመልሰው ሊቋቋሙ ይገባል ብሏል።

የደህንነት ስጋት ያለባቸውን አካባቢዎችም በመለየት የአጭር እና የረዥም ጊዜ እቅዶችን በማዘጋጀት ፈጣን እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባም አሳስቧል።

ከትላንት በስቲያ የደረሰው ጥቃት ማንነትን መሰረት ያደረገ መሆኑን ያስታወሰው መግለጫው በርካታ ሰዎች መሞታቸውን፣ መቁሰላቸውን እና የንብረት ውድመት መድረሱንም ከአካባቢው ባጠናቀረው መረጃ መረዳት ችሏል።

ኢሰመጉ ተጎጂዎችን አባሪ በማድረግ አሰባሰብኩት ባለው መረጃም ጥቃቱ የተፈጸመው ለስብሰባ ትፈለጋላችሁ በሚል የተጠሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተሰበሰቡበት ቦታ መሆኑን ገልፀዋል።

አካባቢው በኮማንድ ፖስት በመከላከያ ሰራዊት የነበረና ጥቃቱ የተፈፀመባቸው ሰራዊቱ አካባቢውን ለቅቆ ከወጣ በኋላ እንደሆነም ያገኘው መረጃ ያስረዳል።

ይህንንም ተከትሎ ማህበረሰቡ የደህንነነት ስጋት እያለባቸው ጥበቃ ሳይደረግላቸው ለዚህ ጉዳት የተዳረጉበትን ምክንያት ኢሰመጉ ለማጣራት ጥረት እንደሚያደርግም አስታውቋል።

በቅርብ ጊዜያት ውስጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የተፈፀሙባቸውን ቦታዎች ወደ ቀደመ ሰላማዊ እንቅስቃሴያቸው በአፋጣኝ እንዲመልስ እና በእነዚህ አካባቢዎች የተፈጠሩትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሚያጣራ ገለልተኛ ቡድን ወደ ሥራ እንዲያስገባ በመግለጫው ጠይቋል።

ኢሰመጉ ለባለፉት ሶስት አስረት አመታት በአገሪቱ ውስጥ የሚከሰቱ ተደጋጋሚ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መሰረታዊ በሚባል ሁኔታ እንዲቀረፍ ሲሰራ የቆየ መሆኑን አስታውሶ ሆኖም ከመንግሥት በኩል የተፈለገውን ውጤት አልመጣም ይላል።

“መንግሥት ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ የመጣውን ዓይነተ-ብዙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በአጭርም ሆነ በረዥም ጊዜ እርምጃ መፍታት የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎችን ከማድረግ ይልቅ ሰበብ በመፍጠር ማለፍ ቀጥሎበታል፡፡” ብሏል።

የአገሪቱ መተዳዳሪያ የሆነውም ህገ መንግሥትም ሆነ አገሪቱ ተቀብላ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶችም ሆኑ ድንጋጌዎች የሰው ልጅ ሰው በመሆኑ ብቻ የማይደፈርና የማይገሰስ ደህንንነቱ በተጠበቀ ሰላማዊ ቦታ በህይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነትና የነፃነት መብት እንዳለው አስታውሷል።

መንግሥት በዋነኝነት እነዚህን መብቶች የማክበር እና የማስከበር ሕጋዊ ተፈጥሯዊ ግዴታዎችን ኃላፊነት እንዳለበትም የኢሰመጉ መግለጫ በተጨማሪ አስፍሯል።

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *