ምንም እንኳን ዓለም አቀፋዊ እና ክልላዊ መገናኛ ብዙሃን እያዩት ያለ ባለ መጠን ለውጥ ቢኖርም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ግን በቅርፅም ሆነ በስራ ሞዴል እንደነበረው ባህላዊ ሆኖ ቀርቷል፡፡ በይዘት ፈጠራ ፣ አቅርቦት እና ክፍያ ትንሽ ነገር ብቻ ነው የተቀየረው፡፡ ቢሆንም ግን ይህ ማለት ምንም ዓይነት ለውጥ የለም ማለት አይደለም፡፡

በኢንተርኔት ላይም አዲስ እና አቆጥቋጭ መገናኛ ብዙሃን እየተነሳ ነው፡፡ ይህም ከተወሰኑ የዜና ጣቢያዎች እስከ ይዘት አጠናቃሪዎች ፣ ከቲዩብ ጣቢያዎች እስከ ቡድን-ተኮር የማህበራዊ ትስስር መረጃ ገጾች ፣ ከቀጥታ ኢንተርኔት ሬዲዮ እስከ ዲጂታል መጽሔቶች ያዳርሳል፡፡ በዚሁ ለውጥ የመገናኛ ብዙሃን ገቢዎችን የማመንጨት ሂደት ላይ ለውጥ ታይቷል፡፡

በአጠቃላይ በአሁኑ ጊዜ እየተንቀሳቀሱ ያሉትን መገናኛ ብዙሃን በሁለት እንከፍላቸዋለን፡ የቆየ /ትውፊታዊ መገናኛ ብዙሃን እና አዲስ መገናኛ ብዙሃን፡፡ የመጀመሪያው ራዲዮ ፣ ቴሌቪዥን እና ጋዜጦችን ሲያካትት የመረጃዎቹ ተጠቃሚ በይዘት ፈጠራው ውስጥ በጣም ትንሽ ተሳትፎ ሲኖረው በሰፊው ዝምተኛ ሆኖ ይታያል፡፡

በተቃራኒው ደግሞ በአዲሱ መገናኛ ብዙሃን የይዘቱ ፈጠራ በሰፊው አሳታፊ ሲሆን የመረጃዎች ክብደት ሰንሰለት ወይም ደረጃ አነስተኛ ነው፡፡ እነዚህ በይዘት ፈጠራ ስራ ላይ ያሉት ልዩነቶች ማለት የሥራ ሞዴሎቹ ይለያያሉ ማለት ነው፡፡

የቆየው መገናኛ ብዙሃን እና አዲሱ መገናኛ ብዙሃን

የቆየው/ትውፊታዊው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃ በስራ ላይ ከተዋወቀበት ጊዜ ጀምሮ በስራ ሞዴሉ ላይ ትንሽ ለውጦችን ብቻ አይቷል፡፡ መቋቋሚያ ገንዘብ የሚገኘው ከመንግስት ሃብት ፣ ከእርዳታ ወይም ደግሞ ከግል ለጋሾች ነው፡፡ ለቴሌቪዥን እና ሬዲዮ መረጃ ፎጆታ በመሳሪያዎች ውስጥ ከሚገኝ ኢንቨስትመንት ውጪ ዋጋ አልወጣላቸውም፡፡ ለጋዜጦች እና መጽሔቶች ዋጋቸው በመሸጫ ዋጋ መልክ ይወጣል፡፡

የቆየው/ትውፊታዊው መገናኛ ብዙሃን ገቢውን ከአባልነት ክፍያ ፣ አመታዊ ፈቃድ ክፍያ (ቴሌቪዥን) ፣ ስፖንሰር ፣ ከድርጅቶች እና ሌሎች ግብአቶች ፣ ከጋራ ወጪ ሽፈና ስምምነት ፣ ከአየር ሰዓት ሽያጭ ፣ ከጋራ ይዘት ፈጠራ ፕሮግራሞች ፣ ከሦስተኛ ወገን ይዘት ስርጭት እና ሌሎችም ያገኛል፡፡ ሆኖም ግን አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከ80 እስከ 90% የሚሆነው ከፍተኛ ገቢ የሚገኘው ከተለመደው ባህላዊ ማስታወቂያዎች ነው፡፡

ጌታቸው ተ. አለሙ የኢትዮጵያ የቆዩ እና ባህላዊ መገናኛ ብዙሃን አዳዲስ የገበያ ጥናት ስልቶችን ፣ ተመልካች እና ተጠቃሚ ጥናቶችን እና የተጠቃሚ ፍላጎቶችን ለሟሟላት ዘርፈ ብዙ መድረኮችን መፍጠር እንዳለባቸው ይናገራል፡፡

አዲሶቹ የመገናኛ ብዙሃን ደግሞ ፍፁም በተለየ የስራ ሞዴል ስራቸውን ያከናውናሉ፡፡ ብዙ ጊዜ የምስረታ ገንዘባቸውን የሚያገኙት ከግል ለጋሾች ነው፡፡ አንዳንዴም እነዚህን የኢንተርኔት የመገናኛ ብዙሃን መድረኮች ለመመስረት ነፃ ይሆናል፡፡ አብዛኞቹ አዲስ መገናኛ ብዙሃን መድረኮች ከሁለት እስከ አምስት ጋዜጠኞች ያሏቸው አነስተና ቡድኖች ናቸው፡፡ ወጪዎች ዌብሳይትን ለመፍጠር ከሚወጣ ወጪ እስከ ለይዘት ፈጠራ የሚወጣ ወጪ ድረስ ሲለያይ ገቢውም በዓይነት እና በመጠን ይለያያል፡፡ ገቢዎች ማስታወቂያዎችን ከመለጠፍ ፣ በአንድ ጠቅታ ክፍያ ፣ የአባልነት ምዝገባ ፣ የክፍያ ገፆች ፣ ድጎማዎች ፣ ስፖንሰርሺፕ እና ወጪ ማጋሪያ ዝግጅቶች ይገኛሉ፡፡ ምንም አንኳን አለም የይዘትን ገንዘብነት ቢረዳም ትርጉሙ ግን በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ከባቢ ዘንድ የሰረፀ አይደለም፡፡ የይዘት ጥራት አነስተኛ እንደሆነ ቀጥሎ ወጥነትም አይታይበትም፡፡ ልዩነት ፣ ሙያዊነት ፣ ሚዛናዊነት ፣ የስነምግባር ክትትል እና ትብብር በመገናኛ ብዙሃን ውስጥ በጣም እያነሱ ነው፡፡ ለምሳሌ፡ ስለ ባለስልጣናት እና ህዝባዊ አካላት ያልተረጋገጠ መረጃን ለማሰራጨት የቲዩብ ጣብያዎችን በስፋት መጠቀም የተለመደ ነው፡፡ ስሜታዊ ርዕሰ አንቀፆች እና በዘገባ ጊዜ ለሁሉም አቅጣጫ እኩል ሽፋን አለመስጠት በህትመት መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች ዘንድ የተለመደ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ከህብረተሰብ ባህል እና ልምዶች ጋር የሚጋጩ ይዘት ያላቸውን (ሙዚቃ እና ፊልሞች) ማሰራጨትም ከስርጭት መገናኛ ብዙሃን ዘንድ የተለመደ ነው፡፡

ጥራት ባለው ይዘት ተጠቃሚዎችን ማገልገል ፈጠራ የታከለበት ይዘት እና የአቅርቦት መንገዶች በሁለቱም የመገናኛ ብዙሃን መድረኮች ብዙም አይታዩም፡፡ በጥቂት ቅርፅ ልዩነት ብቻ አንድ አይነት ይዘት ያላቸው ዜናዎች በሁሉም መድረኮች ሲሽከረከሩ በብዛት ይታያሉ፡፡ ደካማ የይዘት ጥራት ደካማ የመገናኛ ብዙሃን ፋይናንስ አቅምን ይዞ ይመጣል፡፡ ከአስቸጋሪው አካባቢ ጋር ተዳምሮ ከሁለቱም ማለትም ከቁጥጥር እና ከአተገባበር አንፃር ሲታይ የመገናኛ ብዙሃን ትርፍ ዕድገት አስቸጋሪ ነው፡፡ ይህም አብዛኞቹ መድረኮች ከአንድ አመት ባነሰ ጊዜ ከገበያ መውጣታቸውን ተከትሎ ለመገናኛ ብዙሃንን አጭር የህልውና ጊዜ ምስክር ነው፡፡

ከንግዱ እይታ አንፃር በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን እና በአለም አቀፉ የመገናኛ ብዙሃ እድገት መካከል አንድ ክፍተት አለ፡፡ የአለም አቀፉ መገናኛ ብዙሃን ወደ ዘርፈ ብዙ መድረክ ድርጅቶች ሲያድጉ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ግን ባለ አንድ አቅጣጫ መድረክ ብቻ ሆነው ቀርተዋል፡፡ የይዘት አምዶቻቸውን ዘርፈ ብዙ ለማድረግ የሚጥሩ እንደ ፎርቹን ፣ ሪፖርተር ፣ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ፣ ሆርን አፌርስ ፣ አዲስ ኢንሳይት… የተባሉ መገናኛ ብዙሃ ቢኖሩም ሙከራቸው ግን ወጥነት ይጎድለዋል፡፡


በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ማናቸውም የመገናኛ ብዙሃን ድርጅቶች ሁለገብ እና በተግባራዊ መልኩ ተለዋዋጭ የገበያ ስልት የላቸውም፡፡ ስለዚህ ምርቶቻቸውን እና አገልግሎቶቻቸውን ለገበያ የሚያቀርቡት ስሜታቸው በመራቸው መንገድ ብቻ ነው፡፡ በተጨማሪም የተጠቃሚ መረጃን የገበያ ጥረቶችን ለመምራት ምንም ዓይነት ጥረት የለም፡፡ አንዳንዶቹ እንደ Google Analytics ያሉ ከአገልግሎት አቅራቢዎች የተገኙ ትንታኔ ሪፖርቶችን ይቀበላሉ፡፡ ሽያጮቻቸውን ለመምራት ግን አይጠቀሙባቸውም፡፡

ይህ ጉዳይ በቆዩት መገናኛ ብዙሃ ዘንድ ይብሳል፡፡ ይዘት ራሱን ይሸጥ የገቢያቸው ጥረት በሚለጠፉ ማስታወቂያዎች እና በሽፋን ሽያጭ ላይ አያደርጉምና፡፡ አብዛኞቹ የገበያ ጥናት ቡድን የላቸውም ቢኖራቸውም በሙሉ ጊዜ አይሰሩም፡፡ ለይቶ ማውጣት ፣ ማከፋፈል ፣ ዒላማ ማድረግ እና ተጠቃዎችን ማሳተፍ ለአብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን አሁንም ድረስ እንግዳ ነገር ነው፡፡ በውስጣቸው የያዙት አነስተኛ ቁጥር ያለው የገበያ ጥናት ሰራተኛ በበቂ ሁኔታ ያልሰለጠኑ ፣ ባለው ግልፅ የአሰራር መመሪያዎች ያልተካኑ ናቸው፡፡ ስለዚህ ሙከራቸው በአብዛኛው ተናጥላዊ ነው፡፡

የመገናኛ ብዙሃን በደንብ በግብዓቶች አለመታገዝ ለችግር ተጋላጭነታቸውን ከፍተኛ ያደርገዋል፡፡ ስለሆነም የአዳዲስ የአሰራር ዘይቤዎች ሙከራ እና ገቢዎችን ማመንጨት የተለመደ አይደለም፡፡ በደንብ ተንሰራፍቶ የሚገኘው እይታ የተለመደውን አሰራር ተከትሎ ከአደጋ መራቅ ብቻ ነው፡፡ ዕውነታው ግን የተለመደውም አሰራር ቢሆን ከአደጋ የፀዳ አይደለም፡፡
ብዙ ተጠቃሚዎች አብዛኛውን መረጃዎቻቸውን ከማህበረሰባዊ ትስስር ድረ ገፆች እያገኙ በመጡ ቁጥር ይህንን የማህበረሰባዊ ትስስር መገናኛ ብዙሃን ለንግድ ጥናት እንዲሁመ ገቢ ለማስገኛነት መጠቀም በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ቢሆንም ግን ይህንን ማድረግ ፣ የማህበራዊ ትስስር ገፆችን በመገናኛ ብዙሃን የገበያ ንግድ ጥናት ሙከራ ውስጥ በተሳካ ሁኔታ ማስረፅ በይዘት ፈጠራ ፣ ሰራተኛ ቅጥር ፣ የግብዓት አመራር ፣ እና ሌሎች የሥራ ሁኔታዎች ላይ ማሻሻያን ወይም ማስተካከያን ስለሚያስከትል ለመቀበል ቀላል አይደለም (በተለይም ለቆየው የመገናኛ ብዙሃን)፡፡

ወደ ኢንተርኔቱ ዓለም ሙሉ በሙሉ መሸጋገር ብቻውን ለስኬት ማረጋገጫ አይደለም፡፡ የዲጂታሉ ዓለም ስኬት የተሻሉ እና ስኬታማ የሆኑ ስልታዊ ቁጥጥሮች እና በይዘት ፈጠራ ረገድም ክፍት እና አመቺ መሆንን ያካትታል፡፡ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ጊዜው እየተለወጠ መምጣቱን እና የተለመደው የመገናኛ ብዙሃ አሰራር በፋይናንሱ ረገድ ከዚህ በኋላ ሊሰራበት እንደማይችል ልንረዳ ይገባል፡፡ ወደ አዲሱ ዘመን ማስተካከል የመዋቅር እና የፀባይ ለውጥን ከመገናኛ ብዙሃን ድርጅቶች እና ሰራተኞች ይፈልጋል፡፡

የአለም አቀፉ ልምድ እንደሚያሳየው ጊዜው የመገናኛ ብዙሃን ድርጅቶች ወደ ዘርፈ ብዙ መድረክ ድርጅቶች የሚያድጉበት እና በተፈጥሮአቸው አዳዲስ ነገሮችን ወደመሞከር ማደግ አለባቸው፡፡ መገናኛ ብዙሃን የተለመደውን ባህላዊ እና ባለ አንድ አቅጣጫ አቀራረብ ትተው ተጠቃሚዎች በሚፈልጉት መልክ መረጃዎችን አጠናቅሮ ለተለያዩ መድረኮች ግብአት የሚሆኑ ዘገባዎችን መፍጠር ወደሚችል ተቋማዊ መዋቅር መፍጠር አለባቸው፡፡ በተግባራዊነቱም ፅሁፎችን ፣ ፎቶ ፣ ድምፅ ፣ ቪዲዮ ፣ አሳታፊ ገፆችን ፣ ሰበር መረጃዎችን ፣ አጫጭር ዜናዎችን እና ሌሎችንም በአንድነት ፈጥሮ የሚያሰራጭ አሰራር እንዲኖራቸው ያሳያል፡፡ በተጨማሪም የተጠቃሚዎችን ባህሪይ በትንታኔያዊ መሳሪያዎች በመታገዝ በየጊዜው እየተረዱ እና እየተቆጣጠሩ የሚፈልጉትን አይነት ይዘት ያለው መረጃን ማቅረብ ማለት ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ አለመቻል ዜጎችን አስፈላጊ የሚባሉ መረጃዎችን ማሳጣት ሲሆን በፕሮፓጋንዳ እና በተሳሳተ መረጃ ሊሞሉ የሚችሉ ክፍተቶችንም መፍጠር ማለት ነው፡፡

ጌታቸው ተ. አለሙ የኢንቨስትመንት አማካሪ ሲሆን የፎርቹን የቀድሞ ዋና አርታኢም ነበር፡፡ ለአዲስ ስታንዳርድ ፣ ኢትዮጵያ ኢንሳይት ፣ ኢትዮጵያ ኦብዘርቨር እና ለሌሎችም ዘገባዎችን ይሰራል፡፡
selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *