ማይክ ሮበርትሰን አርታዒዎች አንባቢዎቻቸው ህትመቶቻቸውን ፣ የሞባይል መተግበሪያዎችን ወይም ዲጂታል ህትመቶችን በተቻለ አቅም ለረጅም ጊዜ እንዲያነቡና እንዲጠቀሙ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ፅፏል፡፡
የጋዜጦች መጥፋት አይቀሬ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የመጥፊያቸው ጊዜ ፍጥነት በጣም እየጨመረ ነው፡፡ ዋነኞቹ አጥፊዎችም ዲጂታል ወይም የማህበረሰባዊ ትስስር ገፆች አይደሉም፤ ባለቤቶች እና አርታዒዎች እንጂ፡፡ እነሱ ናቸው አንባቢዎቻቸውን የጣሉት እንጂ አንባቢዎች ጋዜጦቻቸውን አልተዉም፡፡
ለምሳሌ ሀገሬን ደቡብ አፍሪካን እንደምሳሌ እንውሰድ፡፡ የዕለታዊ የእንግሊዝኛ ጋዜጦች የፊት ገፆች በባለቤቱ አጠራጣሪ የንግድ ሥራዎች የተሞሉ ናቸው፡፡ የዜና አውታሮችም የሚያበሳጩ ሆነዋል፡፡ ከትክክለኛ ዘገባ ይልቅ ማህበረሰባዊ ትስስር ገፆች ላይ የሚወጡ ጊዜያዊ መርዛማ ጉዳዮች ዙሪያ በማንኛውም ተራ ሰው የተባሉ አሉባልታዎችን ይመግቡን ጀምረዋል፡፡
ሚዛናዊነት ርቆ ከተጣለ ቆይቷል፡፡ አርታዒያን በአንድ ጉዳይ ላይ የመጀመሪያው ሪፖርት ለመሆን ካላቸው ጥድፊያ የተነሳ ትዊተር ላይ የሚገኙትን ጀማሪ የመረጃ ምንጮች ልምድ ካለው ሙያዊ ሥራ መለየት እስኪቅት ድረስ ክፍተት ያላቸውን ዘገባዎች ይዘግባሉ፡፡ ፖለቲካም በቃላት ፍልሚያ ተውጧል፡፡ አነስተኛ ድምፅ ባላቸው ታዋቂ ሰዎች እና የፖለቲካ ሰዎች በማህበራዊ ትስስር ገፆች የሚለጥፏቸው ሀሰተኛ እና ትርጉም የለሽ መረጃዎች በሚቀጥለው ቀን ወደ ህትመት እያመሩ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡
በዚህ የዲጂታል ጊዜ ጋዜጦች በፊት የነበራቸውን አይነት ጥንካሬ እንደማይኖራቸው መቀበል አለብን፡፡ ነገር ግን በራዲዮ እና ቴሌቪዥን መምጣት ጊዜም ይህ እውነት ነበር፡፡ ቢሆንም ጋዜጦች በሚታመን ዘጋቢ የተገመገሙ እና የተረጋገጡ ዜናዎችን የማቅረብ ዋና ጥንካሬአቸው ላይ በማተኮር ይህንን ጊዜ አልፈውታል፡፡ አሁንም መሆን ያለበት እንደዛ ነው፡፡
የአንባቢ ተሳታፊነት ቁልፍ ነገር ነው፡፡ ጋዜጦች ለማደግ አንባቢዎቻቸሁ ጋዜጦቻችሁን ፣ የስልክ መተግበሪያዎቻችሁን እና ዲጂታል እትሞቻችሁን በተቻለ መጠን እያነበቡ ረጅም ጊዜ እንዲያሳልፉ ማድረግ አለባችሁ፡፡ ይህንንም ማድረግ የሚቻለው እንደሚከተለው ነው::
- ስለ እናንተ አይደለም
በመገናኛ ብዙሃን ውስጥ በጣም አስፈላጊ ሰዎች አንባቢዎች ናቸው፡፡ ምን አይነት አንባቢዎች እንደሚኖሩ መለየት ፣ ፍላጎቶቻቸው ምን እነደሆኑ ጥናት ማድረግ እና መረዳት ያስፈልጋል ፣ ከዛም ሥራዎችን የደንበኞችን ፍላጎቶች መሠረት በማድረግ መቅርፅ ፡፡ አርታዒያን እና ባለቤቶች ይመጣሉ ይሄዳሉ ፡ አንባቢያን ሲጠፉ ግን የጋዜጦች ማንነትም አብሮ ይጠፋል፡፡
- ሚናው ምን እንደሆነ ማወቅ
ስኬት የሚመጣው ባለቤቶች ፣ አታሚዎች ፣ እና አርታዒያን ያላቸውን እና መፈፀም ያለባቸውን የተለያዩ ሚናዎች ተረድተው ሲያከብሩ እና እርስ በርስ ሲደጋገፉ ብቻ ነው፡፡ ባለቤቶች አርታኢያንን በአንድ ሚና ላይ መድበው ሥራቸውን በሙሉ ስልጣን እንዲቀጥሉ ያደርጋሉ፡፡ ስኬታማ አርታኢያን ገቢ የማያመነጩ ስያሜዎች እና ምርቶች ጫና ተቋቁመው መዝለቅ እንደማይችሉ ያውቃሉ፡፡ ይህንን ውጥረት እንዴት መፍታት እንደሚቻል ኒው ዮርክ ታይምስ ያስቀመጠው መልስ እስከዛሬ ካጋጠሙኝ የተሻለው ነው፡ የአርትዖት ልህቀት ለትርፋማነት ወሳኝ ነው፣ ትርፋማነት ደግሞ የአርታዒያንን ልህቀት ያስቀጥላል፡፡
- ምን ዓይነት ሥራ ውስጥ እንዳለን መረዳት
ማንኛውም ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክ ያለው ሰው ዜናን ወይም ለዜናው ያለውን የራሱን አረዳድ/ትርጓሜ ማሰራጨት ይችላል፡፡ ስኬታማ መገናኛ ብዙሃን እንዲኖረን የዕውቀት ሥራ ላይ መሰማራታችንን መረዳት አለብን፡፡ ይህም ስኬታማ ሚዲያን ለይቶ ያስቀምጠዋል፡፡
- የአንባቢዎችን ፍላጎት ለይቶ መረዳት
የአንባቢዎችን ፍላጎት ለመረዳት እና ለመወሰን Laddering በጣም ጠቃሚው የጥናት/ምርምር ዘዴ ነው፡፡ መሠረቱ ለምን ? የሚሉ ጥያቆዎችን ደጋግሞ መጠየቅ ነው፡፡ ጋዜጣ ለምን ያነባሉ? በየቀኑ? በሳምንት? ይህንን ጋዜጣ? መልሶቹ የሚከተሉትን ነገሮች በግዴታ ያሟላሉ ዕምነት – “ጋዜጣውን የማነበው የተፃፈው ነገር እውነት እንደሆነ ስለማምን ነው”ዕውቀት – “ዕውቀት ስለሚያስጨብጠኝ እና አንድ ርምጃ ስለሚያራምደኝ ጋዜጣውን አነባለሁ”
ቤተሰብ – አንድ ርምጃ መራመድ የምፈልገው ለቤተሰቤ ማሟላት ያለብኝ ነገር ማቅረብ ስለምፈልግ ነው፡፡ በተጨማሪም ይህ ጋዜጣ ወላጆቼ ፣ ባለቤቴ ፣ ልጆቼ ፣ ልጅ ልጆቼ ሊደሰቱባቸው የሚችሉ ጉዳዮችን ወይም አምዶችን ይዟል፡፡ መዝናኛ – ይህ ጋዜጣ ስለሚያዝናናኝ አነበዋለው፡፡ በትርፍ ጊዜዬ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ኃሳብ ይሰጠኛል ፣ ያስቀኛልም፡፡
- በጥልቀት መጠየቅ
ተመሳሳይ የደረጃ መጠይቅ ዘዴን በመጠቀም ነገሮችን በጥልቀት ለመረዳት ጥያቄዎችን መጠየቅ፡፡
ምን ዓይነት ዕውቀት? የቤተሰብዎ አባላት ስለምን ማወቅ ይፈልጋሉ? ምን ያዝናናዎታል? ከልምዴ በመነሳት በጋዜጦች የተዘነጉ የአንባቢያን ፍላጎት ጉዳዮች ፡ ስለ ሃገሩ መንግስት ፣ ትምህርት ፣ ጤና ፣ ንብረት እና ሰዎች የሚፈልጓቸው ታሪኮች (የተሻሉት በፍርድ ቤቶች ውስጥ ይገኛሉ) ዘገባዎች ናቸው፡፡ በእድሜ የገፉ ሰዎች ፍላጎት አብዛኛውን ጊዜ ሙሉ በሙሉ ችላ ይባላል፡፡ ምንም እንኳ በጣም ሀብታም ቢሆኑም ረጅም ጊዜ የሚኖሩት ተግተው የሚያነቡት ናቸው፡፡
- አክብሮት
ሌሎች የዜና ማሰራጫዎች በሚያሰራጩት ሀሰተኛ ዜናዎች ዝናን ሲያገኙ ጋዜጦች ግን የሚያውቁትን እውነት ብቻ በማተም ራሳቸውን መለየት አለባቸው፡፡
የፕሬስ ኮድ ካለ ሰራተኞች ህጎቹን አውቀው መሰልጠን እና ማክበር አለባቸው፡፡ ከሌለ ደግሞ ሊኖር ያስፈልጋል፡፡ የፕሬስ ኮድ የሚኖረው የአንባቢዎችን ፍላጎት ለመጠበቅ ሲባል ቢሆንም በስተመጨረሻ ግን ጋዜጦችን ለመጠበቅ ነው፡፡ በኮዱ ለመመራት ማንገራገር አያስፈልግም፡፡ ሊኮራበት ያስፈልጋል፡፡ ከሌሎች ሀሰተኛ ምንጮች ይለያልና፡፡
ጥብቅ ትክክለኛነትን ማረጋገጫዎችን ማስተዋወቅ – የአሜሪካን ጋዜጦች ከፍተኛው ጥናት የሰው ስሞች እና እድሜዎችን የመሳሰሉ መሰረታዊ እውነታዎችን በትክክል አለማወቅ ወይም አለመጥራት የአንባቢዎቻቸውን እምነት እንዲያጡ ዋነኛው ምክንያት ነበር፡፡
ከፍተኛ አርታዒያን የመጨረሻ አራሚዎች መሆን አለባቸው፡፡ እንደ፡ ምንጩ ማነው? ውጤቶችን ለማስተካከል መጠቀሚያ እየሆንን ነው? ይህንን ታሪክ ለምንድን ነው የምንዘግበው? የህዝቡን ፍላጎት ያማከለ ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ማረጋገጥ አለባቸው፡፡
ቅሬታዎችን ከማስተናገድ በተጨማሪ በዘገባ ውስጥ የተጠቀሱ ወይም ንግግራቸው የተጠቀሰላቸውን ሰዎች በየሳምንቱ እያገኘ ዘገባው ላይ ጥያቄ ካላቸው ወይም ችግር ካለበት የሚያጣራ የአንባቢ አርታዒ ማስቀመጥ ይጠቅማል፡፡
ነገር ግን በትክክል መረዳት የመጀመሪው ርምጃ ነው፡፡ የኋላ ታሪኩን እና ከነባራዊው ሁኔታ ጋር መግጠሙን ማረጋገጥም ያስፈልጋል፡፡ አንባቢዎች ስለጉዳዩ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ መጥቀስን ጨምሮ ለምን እንደተከሰተ በደንብ ሳይብራራ እና መፍትሔ አብሮ ካልቀረበ ከዚህ በኋላ ችግር እንዳለ መጠቆም ብቻውን በቂ አይሆንም (ለምሳሌ በመንግስት ውስጥ ያለ ሙስና) ፡፡
በተጨማሪም አክብሮት ማለት ባለቤቶች ፣ አታሚዎች ፣ አርታዒያን እና ጋዜጠኞች አስፈላጊ ሆኖ ያገኙት ነገር አንባዎች አስፈላጊ ነው ብለው የሚያስቡት ነገር ላይሆን እንደሚችል መረዳት ነው፡፡ ለመታዘዝ ጥሩ ልምምድ የለንደን ሰንዴይ ታይምስ የቀድሞው አርታኢ የሆነው ሃሮልድ ኢቫንስ ያለው ነው፡ ከበድ ያሉ ርዕሰ ጉዳዮችን ታዋቂ በሆነ ሁኔታ ያክብሩ እና ታዋቂ የሆኑ ርዕሰ ጉዳዮችን አክብደው ያክብሩ፡፡
- ዘገባን በደንብ ማስረዳት
ምንም ያህል የጋዜጣው ይዘት ጥሩ ቢሆንም አንባቢዎች በደንብ እንዲረዱት ቀለል ተደርጎ ካልተገለፀ አንባቢዎችን ማግኘት አይቻልም፡፡ ጥረቶችን በሚከተሉት ነጥቦች ላይ ማድረግ ያሻል፡፡
- ታሪኮችን በተቻለ አቅም በጥሩ ሁኔታ ማቅረብ፡፡
- የተቻለውን ያህል ለታሪኩ ግብአት የሚሆኑ ነጥቦችን ማግኘት፡፡ ሰዎች ጊዜ ያጥራቸዋ፡፡ የተቻለውን ያህል መረጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ እና በፍጥነት ማግኘት ይፈልጋሉ፡፡
- ፍጥነት – አንባቢዎች ፍላጎታቸውን ይዘው እንዲቀጥሉ የአጫጭር እና የረጃጅም ታሪክ ቅይጦችን ማቅረብ፡፡
በመጨረሻም፡ አዳዲስ ነገሮችን ለመሞከር መፍራት አያስፈልግም፡፡ በተጨማሪም ግን የአንባቢያንን ይሁንታ ያላገኙ አዳዲስ ነገሮችንም ለመተው ማንገራገር አያሻም፡፡ ዲጂታል ሚዲያው ከአንባቢያን ጋራ ለመገናኘት ተግባራዊ ያደረገውን ፈጠራ መጠቀም አለብን፡፡ የሚሰራው ጥናት አንባቢዎች ጋዜጣችንን እያነበቡ ከአንድ ሰአት በላይ እንደቆዩ ሲያሳየን ያኔ ሚዲያው ስኬታማ ወይም አሸናፊ መሆኑን እንረዳለን፡፡
ማይክ ሮበርትሰን የደቡብ አፍሪካው ከፍተኛ ተነባቢ ጋዜጣ ዘ ሰንዴይ ታይምስ የቀድሞ አርታዒ እና የ Times Media Limited የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ነበር፡፡ በተጨማሪም የወቅቱ Tiso Black- star, the owners of The Sunday Times, Business Day, Financial Mail, Timeslive, The Sowetan, Sunday World, The Herald and Daily Dispatch አርታዒ ነው፡፡