ከፌስቡክ፣ ከቴሌግራም ቻናልና ከሌሎች ማህበራዊ ድረ ገፆች ላይ ከ200 በላይ የሚሆኑ ግለሰቦችን ፎቶግራፍ በማውረድ እና ልዩ ልዩ የማቀናበሪያ ሶፍት ዌሮችን በመጠቀም ከአንገት በላይ ያለውን የፊት ገፅታቸውን ቆርጦ በማቀነባበር የተለያዩ አስነዋሪ ድርጊቶችን ሲፈፅሙ የሚያሳዩ ፎቶዎችን በፌስቡክ፣ በቴሌግራም እና በኢሞ ለቋል የተባለውን ግለሰብ የድርጊቱ ሰለባ ከሆኑት ሰዎች በደረሰው ጥቆማ መሰረት ተጠርጣሪውን ድርጊቱን ለመፈጸም ሲጠቀምባቸው ከነበሩ ኮምፒተር እና የሞባይል ስልክ ጋር ይዞ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የጉዳዩ መርማሪ ሳጅን አያሌው ጌታቸው ገልፀዋል።
ምርመራውን ለማስፋትና ተጨማሪ ማስረጃዎችን ለማሰባሰብ ተጠርጣሪው የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆበት በእስር ላይ እንደሚገኝ እና ወጣት ሴቶች፣ ህፃናት፣ አባወራዎች እና እማወራዎች በግለሰቡ ድርጊት ሰለባ መሆናቸውን መርማሪው ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ተጠርጣሪው ድርጊቱን መፈፀም ከጀመረ መቆየቱን፤ ፎቶግራፋቸውን ከተለያዩ ማህበራዊ ድህረ ገፆች ላይ በመውሰድ አስነዋሪ ድርጊት እንደፈፀሙ በማስመሰል በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በመልቀቁ ለማህበራዊ እና ስነ-ልቦናዊ ጉዳት መዳረጋቸውን በቤተሰብ እና በጓደኞቻቸው አመኔታን እንዳጡና ትዳራቸው የፈረሰባቸው መኖራቸውን፣ ከስራ እንደተባረሩ፣ የተደፈረች ወጣት መኖሯን ያነጋገርናቸው የግል ተበዳዮች አስረድተዋል፡፡
ግለሰቡ ህገ-ወጥ ተግባሩን የሚፈፅመው የተመልካች ቁጥር በማብዛት በህገ-ወጥ መንገድ ገንዘብ ለማግኘት ካለው ፍላጎት መሆኑን ሳጅን አያሌው እና የድርጊቱ ሰለባዎች ጠቁመው ገቢ ለማግኘት በሚል ኃላፊነት በጎደለው መንገድ ማህበራዊ ድህረገፆችን ላልተገባ ተግባር የሚጠቀሙ ግለሰቦች ድርጊታቸው ከግለሰቦች አለፍ ሲል ሀገርን የሚጎዳ መሆኑን በመረዳት ከህገወጥ ተግባራቸው ሊታቀቡ ይገባል ብለዋል፡፡
ከ200 በላይ ሰዎች በግለሰቡ ድርጊቱ ጉዳት እንደደረሰባቸው ፖሊስ አስታውቋል፡፡
በመጨረሻም ተመሳሳይ ችግር ያጋጠማቸው እና ለፖሊስ ሪፖርት ያላደረጉ ግለሰቦች ፖሊስ ዘንድ በመቅረብ ሊያመለክቱ እንደሚገባ መርማሪው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡