በነጻነት ለመናገርና ለመደራጀት የማህበራዊ ሚድያው ለኢትዮጵያውያን የፈጠረው መድረክ ቢኖርም ለወንጀል እንዲሁም የንግድና ፖለቲካ ስጋቶች ተጋላጭ አድርጓቸውል። እንደ ሌሎች ሃገሮች ሁሉ ኢትዮጵያ ውስጥ የማህበራዊ ሚድያው መምጣት ግለሰቦችና ህዝብ የሚገናኙበትን እና ሃሳብ የሚለዋወጡበትን መንገድ በእጅጉ ቀይሮታል። ስለነዚህ ለውጦች ከማብራራት በፊት የኢትዮጵያ የኢንተርኔት አድማስ ምን እንደሚመስል መቃኘት ያስፈልጋል። በየካቲት 2011 ዓ.ም ወደ 35.4 ሚሊየን የሚጠጉ የሞባይል ተጠቃሚዎች እንዳሉ የታወቀ ሲሆን ከነዚህም ግማሽ ሚሊየን የሚሆኑት የሞባይል ዳታ ተጠቃሚ ናቸው። ከ14.1 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ የብሮድባንድ ተጠቃሚዎች ያሉ ሲሆን 4.3 የሚሆኑት ደግሞ ናሮው ባንድ የሚባለውን የአነስተኛ ኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ ናቸው። በአጠቃላይ ሃገሪቷ ውስጥ ከሚገኘው 108 ሚሊየን ህዝብ ወደ 19.2 የሚጠጉ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች አሉ። የኢንተርኔት ግንኙነት ላይ ስላለው ጥራት መረጃዎችን መሰብሰብ አስቸጋሪ ቢሆንም ጥናቶች እንደሚያሳዩት ግን የግንኙነት ጥራቱ በየዓመቱ በ27 በመቶ መሻሻል እያሳየ ይገኛል። በእርግጥ ሁሉም 19 ሚሊየኑ ህዝብ አስተማማኝ የኢንተርኔት አገልግሎት ያገኛል ወይም ኢንተርኔትን በተመሳሳይ መንገድ ይጠቀማል ማለት እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል።
ሰዎች እንዴት ኢንተርኔት እንደሚያገኙ ከጠቀስን በኋላ የማህበራዊ ሚድያውን ማን እንደሚጠቀመው ማየት አስፈላጊ ነው። በ 2010 ዓ.ም ከ 4 ሚሊየን ያነሱ የማህበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች የነበሩ ሲሆን 3.6 የሚሆኑት በዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ስልኮች የሚጠቀሙ ናቸው። በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ይህ ቁጥር ከ 50 በመቶ የበለጠ እድገት አሳይቷል። ኢትዮጵያ ውስጥ በጥር 2011 ዓ.ም ከ 19 ሚሊየኑ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ወደ 6.1 ሚሊየን የሚጠጉ የማህበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች ያሉ ሲሆን ከነሱም ውስጥ 5.6 ሚሊዮን የሚሆኑት በተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው ኢንተርኔትን የሚጠቀሙ ናቸው። ይህም የሚያመለክተው ተንቀሳቃሽ ስልኮች ለኢትዮጵያ የማህበራዊ ሚድያ ግንኙነቶች የጀርባ አጥንት የመሆናቸውን ሃቅ ነው። ከሌሎች ሃገሮች ጋር በሚመሳሰል መልኩ ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው የማህበራዊ ሚድያ አማራጭ ፌስቡክ ሲሆን 6.1ሚሊየን ተጠቃሚዎችም አሉት። ኢንስታግራም በ 360,000 ተጠቃሚዎች ሲከተል ትዊተር ደግሞ 70,000 ተጠቃሚዎች ብቻ አሉት። ከ70 ፐርሰንት በላይ የሚሆኑት የፌስቡክ እና ትዊተር ተጠቃሚዎች ወንዶች ሲሆኑ የተቀረውን ድርሻ የያዙት ሴቶች ናቸው። ለኢንስታግራም ግን 36 በመቶ የኢንስታግራም አድራጊዎች ሴቶች ሲሆኑ 64 በመቶ የሚሆኑት ወንዶች ናቸው። በተጨማሪም አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት የማህበራዊ ሚድያው ተጠቃሚዎች ከ25-34 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው። ስለዚህም አብዛኛው የኢትዮጵያ ማህበራዊ ሚድያ ተጠቃሚ በከተሞች የሚገኙ ወጣት ወንዶች ናቸው ማለት ይቻላል። እንደሌሎች የማህበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች ሁሉ ኢትዮጵያውያንም ማህበራዊ ሚድያውን የሚጠቀሙት በተለይ ከጓደኞቻቸው ጋር ለመገናኘት፣ መረጃዎችን ለማጋራት እና ለዜና ነው። ነገር ግን ከሌሎች ሃገራት በተለየ መልኩ የኢትዮጵያ መንግስት እርምጃዎች የማህበራዊ ሚድያውን እውቅናና ዕድገት ተጽዕኖ እያሳደረበት ይገኛል። ተቀባይነት ያላገኘውን የ 1997 ዓ.ም ምርጫ ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት እንደ ጸረ-ሽብር አዋጅ ቁ 652/2009፣ የሚድያ ነጻነት እና የመረጃ አጠቃቀም አዋጅ ቁ 590/2008 ፣ የብሮድካስት አገልግሎት አዋጅ ቁ 533/2007, የ ኮምፒተር ወንጀሎች ህግ እንዲሁም ሌሎች ነጻ ፕሬስን እና ሃሳብን የመግለጽ ነጻነትን የገደሉ ህግጋቶችና ድንጋጌዎችን አውጥቷል። እነዚህ ህጎችም የህትመት ፕሬሶች እንዲዘጉ፣ የግል ሚድያዎች ሳንሱር እንዲደረጉ፣ ጋዜጠኞች እንዲሰደዱ እንዲሁም ብዙዎች እንዲታሰሩ አድርገዋል። እነዚህ ተግባራትም በብሔራዊ ሚድያዎች መንግስትን ብቸኛው ‘የእውነተኛ’ መረጃ ምንጭ በማስመሰል ተራውን ዜጋም ሆነ አክቲቪስቶችን እንዲሁም ሌሎች አማራጭ የመረጃ ምንጮችን የሚፈልጉ ሰዎችን ወይም ከመንግስት አጀንዳ ውጪ ስለሆኑ ነገሮች ለማወቅ የሚፈልጉትን ወደ ማህበራዊ ሚድያ ፊታቸውን እንዲያዞሩ አድርጓል። ብዙዎችም ማህበራዊ ሚድያውን ተጠቅመው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚስተዋሉ የዕለት ተዕለት ትግሎችን እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በማሳየት በመንግስት ብቻ የሚቀርበውን የአንድ ወገን ንግርት ተገዳድረዋል። #OromoProtests፣ #AmaharProtests፣ #StopCensorship፣ እንዲሁም ሌሎች መንግስትን እና የመንግስት መዋቅርን ሲፈትኑ ከነበሩት ስመጥር ሃሽታጎች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው። የማህበራዊ ሚድያው ለበርካታ ኢትዮጵያውያን የመናገር ነጻነትን ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም ይህን ነጻነት የሚገዳደሩ ጉዳዮች ግን አልጠፉም። እንደ አብዛኛዎቹ አምባገነን መንግስታት ሁሉ የኢትዮጵያ መንግስት በኢንተርኔት የሚካሄደውን የሃሳብ ልውውጥ በመቆጣጠር ሃሳቦች ላይ ተጽእኖ ለማሳደር ሞክሮ ነበር። የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ቢያንስ በቀድሞው መንግስት ስር ሳንሱር ለማድረግ ብሎም ስለ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሚያወሩትን፣ የተቃውሞ ጥሪ እና ቅሬታዎችን የሚያቀርቡትን ለማሰር የአክቲቪስቶችን፣ የጋዜጠኞችን፣ የተቃዎሚ ቡድኖችን እንዲሁም የግለሰቦችን የማህበራዊ ገጾች ይከታተል ነበር። በቀድሞው መንግስት ትዕዛዝ ብዙ ሰዎችም በማህበራዊ ሚድያ ባጋሯቸው ነገሮች የተነሳ ታፍነዋል፣ ተሰቃይተዋል እንዲሁም ታስረዋል። ከሁሉም የሚታወሰው ድርጊት ደግሞ ዮናታን ተስፋዬ ልይ ሽብርተኝነትን አበረታተሃል በሚል የደረሰበት ክስ ነበር። ከተወሰነ ግዜም በኋላ ክሱ ተለውጦ አመጽ በማነሳሳት ወንጀል በጸረ-ሽብር አዋጅ ሳይሆን በወንጀለኛ መቅጫ እንዲዳኝ ተደርጎ ነበር።
ከዚህም በተጨማሪ የቀድሞው መንግስት የማህበራዊ ሚድያ ዘጋቢዎች በመቅጠር እንደ መደበኛ ኢንተርኔት ተጠቃሚ ሆነው ገዢውን ፓርቲ እንዲያወድሱ እንዲሁም በመንግስት የሚነገሩ ነገሮች ጋር የማይስማሙ ሰዎችን እንዲያጠቁ እና እንዲያንቋሽሹ አድርጓል። ነገር ግን የአብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣት እና የአዲስ መንግስት መፈጠር ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የማህበራዊ ሚድያ መልክ ቀይሮታል።በማህበራዊ ሚድያ ለመሳተፍ ይፈሩ የነበሩ ብዙሃን ሰዎች አሁን የኢንተርኔት መድረኩን ለመጠቀም ተበረታተዋል። ማህበራዊ ሚድያውን ዜጎችን ለመሰለል እና ሃሳባቸውን እንዳይገልጹ ለማስፈራራት ዓላማ ይጠቀመው የነበረው መንግስት አሁን እራሱ በማህበራዊ ሚድያው ላይ ንቁ ተሳታፊ ሆኗል። እንደምሳሌም ቀድሞ ለዜና የሚበቁ የመንግስት ሃሳቦች በብሔራዊ የቴሌቭዢን እና ሬድዮ ጣቢያዎች ይቀርቡ የነበረ ሲሆን አሁን ግን ጠቅላይ ሚንስትሩ፣ ቃል ዓቀባያቸው፣ የጽ/ቤታቸው ባልደረቦች እና ሌሎች ቁልፍ የመንግስት ሰዎች ማህበራዊ ሚድያውን በተለይም ፌስቡክ እና ቲውተር በመጠቀም ለህብረተሰቡ የሚነገሩ በሃገሪቷ ውስጥ እየተካሄዱ ያሉ ነገሮችን በማሳወቅ ላይ ናቸው። ይህ ድርጊትም በመንግስት ስር ያሉትንም ሆነ በግል የሚንቀሳቀሱትን ሚድያዎች በእኩል ደረጃ ዜና እንዲያገኙ በማድረግ የተደላደለ የመጫወቻ ምህዳር ፈጥሮላቸዋል ነገር ግን መንግስት የማህበራዊ ሚድያውን መጠቀሙ ለሚድያው የተደላደለ መስክ ቢፈጥርም አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ከኢንተርኔት አገልግሎት ውጪ በመሆኑ መንግስት የኢንተርኔት ተጠቃሚ የሆኑ ዜጎች እንደሚያገኙት አይነት መረጃ ለሌሎችም እንዲደርስ ማድረግ አለበት። ያልተገባ የማህበራዊ ሚድያ አጠቃቀም በቅርብ እና በሩቅ ካሉ የኢትዯጵያ ጎረቤቶች አንጻር ኢንተርኔት ላይ ጥሶ የመግባት (ፔኔትሬሽን) አሃዝ እና ማህበራዊ ሚድያው ላይ ያለው የኢትዮጵያውያን ተሳትፎ በጣም ዝቅተኛ ነው። ምንም እንኳ ይህ ቁጥር ከሌሎች ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ቢሆንም የማህበራዊ ሚድያው ተግዳሮቶችና ጥቅሞችም በሃገሪቷ ውስጥ እየተስተዋሉ ነው። የማህበራዊ ሚድያው ብዙዎች ድምጻቸውን እንዲያሰሙ እና ሃሳባቸውን እንዲገልጹ ብሎም ኢንተርኔት ላይም ሆነ ከዛ ውጪ እንዲደራጁ እንደማስቻሉ ሁሉ እውነተኛነታቸው ያልተረጋገጡ እንዲሁም ሃሰተኛ የሆኑ መረጃዎችን ጭምር እንዲሰራጩ አድርጓል።በዕኩይ ተግባራት፣ ለማህበራዊ ሚድያ መድረኮች እና በሌሎችም ምክንያቶች የተጠቃሚዎች የግል መረጃ ባልተገባ መልኩ ጥቅም ላይ ውሏል። ያልተረጋገጡ መረጃዎች እና ሃሰተኛ መረጃዎች ቴክኖሎጂ በተለይም የማህበራዊ ሚድያው በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ሃሰተኛ መረጃ እድዲሰራጭ ጥቅም ላይ ሲውል ቆይቷል። ያልተረጋገጠ መረጃ ባለማወቅ የሚሰራጭ የማያስተማምን መረጃ ሲሆን ብዙውን ጊዜም ሚድያው የተሳሳተ መረጃን ሲዘግብ ወይንም ገለልተኛ በሆነ መንገድ ያልተረጋገጠ መረጃን ሲያቀርብ የሚፈጠር ነው። ሃሰተኛ መረጃ ደግሞ ህብረተሰቡ የተሳሳተ መንገድን እንዲይዝ ሆን ተብሎ የሚሰራጭ ከሃቅ የራቀ መረጃ ነው። ያልተረጋገጠ መረጃና ሃሰተኛ መረጃ አዲስ ክስተት ባይሆንም በዲጂታል ዘመን ግን በሚልዮን የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎች በአንድ ግዜ መረጃዎችን በኢንተርኔት መለዋወጥ በመቻላቸው ያልተረጋገጡ እና ሃሰተኛ መረጃዎች መጠነ ሰፊ ተጽዕኖዎችን ማሳደር ችለዋል። አሳሳች እና ከእውነት የራቁ ሃሳቦችን በሚያመርቱ ማሽኖች፣ ለተመረጡ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚደርሱ ለፖለቲካ ፍጆታ የሚውሉ ማስተዋወቂያዎች፣ ጥራትንም ሆነ እውነታን ያላገናዘቡ ተዛማች ሃሳቦችን የሚፈጥሩ ስሌቶች (አልጎሪዝሞች) ያልተረጋገጡ መረጃዎችን እና የሃሰተኛ መረጃዎችን ተጽዕኖ ሲያጎሉ ቆይተዋል። ከላይ የተጠቀሱት መንሰኤዎች እና ሌሎችም የማህበራዊ ሚድያውን መራጮች ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር እና ምርጫ ለማሸነፍ ተግባር የሚውል አዲሱ የጦርሜዳ አድርገውታል። ለምሳሌም እ.ኤ.አ በ 2017 በተካሄደው የኬንያ ምርጫ ፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ዋትስ አፕ እና ዩቲውብ በምርጫ ቅስቀሳዎች ወቅት መሪ ተጫዋቾች ነበሩ። የፖለቲካ ፓርቲዎችም ብዛት ያለው ህዝብ ጋር ለመድረስ፣ ቅስቀሳቸውን ለማካሄድ ብሎም ጥላቻና መፈራራትን ለመዝራት እነዚህን መንገዶች ተጠቅመዋል። መደበኛው ሚድያ ለሃሰተኛ መረጃ የተጋለጡ አሳሳቢ ጉዳዬች ላይ በበቂ ሁኔታ ሽፋን መስጠት፣ ማረጋገጥ እና መዘገብ ሲያቅተው የ ቢቢሲ፣ ሲኤንኤን፣ ኤን ቲቪ እና ሌሎችም አርማዎች ያሉባቸው ሃሰተኛ መረጃዎችን የያዙ ቪድዮዎች በማህበራዊ ሚድያው ላይ በስፋት ተበትነው ነበር። በኢትዮጵያ ሁኔታ ደግሞ የሰኔ 16 ፣ 2010 ዓ.ም የመስቀል አደባባዩ የቦምብ ጥቃት ከፍተኛውን ቁጥር ያስተናገደ ያልተረጋገጠ መረጃ እና ሃተኛ መረጃ የተዛመተበት ክስተት ሳይሆን አይቀርም።ብዙዎች ጥቃቱን ያደረሱ ናቸው በሚል እውነተኛነታቸው ያልተረጋገጠ ፎቶዎችን በማህበራዊ ሚድያዎች በማጋራት ለብዙሃን ፍትህ ሲጠይቁ የነበረ ቢሆንም ዘግይተውም ቢሆን እነዚህ ሰዎች እራሳቸው የአደጋው ተጠቂ የነበሩ ንጹሃን ዜጎች መሆንቸውን ተገንዝበዋል። የመደበኛ ሚድያውም ያልተረጋገጡ እና ሃሰተኛ የሆኑ መረጃዎችን ከማራገብ ቢቆጠብም እነዚህን በማህበራዊ ሚድያው የተዛመቱትን ያልተረጋገጡና ሃሰተኛ መረጃዎች መቀልበስ የሚችሉ ተዓማኒነት ያላቸው መረጃዎችን ማቅረብ ሳይችል ቀርቷል።
ያልተገባ የዴታ /ጥሬ መረጃ/ አጠቃቀም የሶሻል ሚድያ አገልግሎት አቅራቢዎች አገልግሎቶቻቸውን ለተጠቃሚዎች በነጻ ለማቅረብ በቢሊየኖች የሚቆጠሩ ዶላሮች ወጪ ያደርጋሉ። የንግድ አሰራር /ቢዝነስ ሞዴላቸውም የተጠቃሚው ዴታ / ጥሬ መረጃ ላይ የተመሰረተ ነው – ተጠቃሚዎች እና ስለነሱ ያለው መረጃ እንደ ምርታቸው ነው። ስለ ተጠቃሚዎች ያለው ጥሬ መረጃ እና የግል መረጃዎች ለማስታወቂያ ገበያው በጥቅል ይሸጣሉ ለዚህም ነው ብዙዎች ዳታን ወይም ጥሬ መረጃን አዲሱ ነዳጅ ሲሉ የሚጠሩት። ቀለል ያለ ምሳሌ ለመስጠት ያህል ፌስቡክ ላይ ሰዎች የወደዷቸው ነገሮች፣ ያጋሯቸው ልጥፎች፣ ምስሎች፣ ታግ ያደረጓቸው ቦታዎች፣ የሄዱባቸው ቦታዎች፣ የፌስቡክ ጓደኞቻቸው፣ የተለዋወጧቸው የግል ውይይቶች እና ሌሎችም በማህበራዊ ሚድያው ላይ ያካሄዷቸው ክንውኖች ሁሉ የጥሬ መረጃ ነጥቦች /ዴታ ፖይንት/ ናቸው። እነዚህ የጥሬ መረጃ ነጥቦች ባልተገባ መልኩ ለማስታወቂ ድርጅቶች በመሸጥ አስተዋዋቂዎች መድረስ የሚፈልጉትን ተጠቃሚ ኢላማ ውስጥ እንዲያስገቡበት ወይም ለፖለቲካ ፍጆታ ያለ ተጠቃሚው ፈቃድ ጥቅም ላይ ይውላሉ። በዓለም ዙሪያ ያሉ መንግስታት ቀስበቀስእነዚህ አገልግሎቶች የሚሰሩባቸውን መንገዶች እያወቁ እና የጥሬ መረጃ /ዴታ አጠባበቅን አሳሳቢነት፣ ያልተገባ የዴታ አጠቃቀምን፣ የግለሰብ ሚስጥርን ከመጠበቅ ጋር ያሉ ጉዳዮችን ብሎም የማህበራዊ ሚድያውን የተቆጣጠሩትን የውድድር እና የመተማመን ጸር የሆኑ ተግባራትን እየተረዱ መጥተዋል። ወደ 87 ሚሊየን የሚጠጉ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች (አብዛኛዎቹ በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ) ሰለባ የሆኑበት የካምብሪጅ አናሊቲካ ቅሌት የተባለው ፌስቡክ ያለፈቃዳቸው ካምብሪጅ አናሊቲካ ለተባለኩባንያ የተጠቃሚዎችን መረጃ አሳልፎ በሰጠበት ግዜ ነበር። ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ የሚገኘው ካምብሪጅ አናሊትካ የፌስቡክ ተጠቃሚዎችን መረጃ በመጠቀም የፖለቲካ ማስታወቂያዎችን ለየተጠቃሚው እንዲሆን አድርጎ ሲያዘጋጅ አብዛኛዎቹም ዶናልድ ትራምፕን ለማገዝ የተቀነባበሩ ነበሩ።
የእነዚህ ማስታወቂያዎች አላማም መራጮች ወይ ዶናልድ ትራምፕን እንዲመርጡ ወይም ጭራሹን ከመምረጥ እንዲቆጠቡ ማድረግ ነበር። ይኸው ኩባንያም ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና ምክትል ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ሁለት ግዜ እንዲመረጡ አግዟል። በእርግጥ ይህ ኩባንያ የኬንያ መራጮች ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ከፌስቡክም ሆነ ከሌላ ማህበራዊ ሚድያ መረጃ ባይሰበስብም የጥላቻ እንቅስቃሴዎችን ለማዛመት፣ ኢንተርኔት ላይ የሚካሄዱ ብዙውን ጊዜም ከኢንተርኔት አልፈው የሚሄዱ የሃሳብ ልውውጦችን ደንበኞቹን በሚጠቅም መልኩ ለመመረዝ ፌስቡክ፣ ዩቱውብ እና ሌሎች የማህበራዊ ሚድያ አማራጮችን ተጠቅሟል። የተለያዩ የፌስቡክ ልጥፎች፣ ተጠቃሚዎች የሚወዷቸው ገጾች፣ ተጠቃሚዎች የሚሳተፉባቸው ነገሮች ይዘት ወይም ብዙዎች ተራ ነገር የሚመስሏቸው የኢንስታግራም ምስሎች ተጠቃሚዎች ያላቸውን የመረጃ አጠቃቀሞች ለመረዳት፣ ከኢንተርኔት ውጪም ስለሚገዟቸው ነገሮች በተለይ ባልተገባ መልኩ ደግሞ የምርጫ ድምጽ አሰጣጣቸውን ሁሉ ለመረዳት ይውላሉ። መረጃን ከመከላከል እና የግለሰብ ሚስጥርን ከመጠበቅ ጉዮች በተጨማሪ እነዚህ በአገልግሎት ሰጪዎቹ የሚደረጉ ድርጊቶች፣ ለነዚህ ተግባራት ሲባል የተጠቃሚዎችን መረጃ የሚጠቀሙ ሶስተኛ ወገኖች እና እነዚህን አገልግሎቶች የሚገዙ ደንበኞች ሁሉም የስነ-ምግባር ጉድለት ያለባቸው ሲሆኑ እንደውም በ 21ኛው ክፍለዘመን ዲሞክራሲ ከተጋፈጣቸው ትልልቅ ተግዳሮቶች አንዱ ሳይሆኑ አይቀሩም። በአጠቃላይ ማህበራዊ ሚድያ በኢትዮጵያም ሆነ በተቀረው ዓለም ሰዎች መረጃን የሚቀበሉበትን መንገድ፣ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችን በኢንተርኔትም ሆነ ከዛ ውጪ የሚያካሂዱበትን እና እንደ ህዝብም እንደ ግለሰብም የሚፈጥሯቸውን ግንኙነቶች ለውጠዋል። የቀድሞውና የአሁኑ መንግስት ኢንተርኔትን በመዝጋት፣ የማህበራዊ ሚድያ ገጾችን በማገድ እንዲሁም በሞባይል ዴታ ኢንተርኔትን በማቋረጥ የማህበራዊ ሚድያውን አዎንታዊም አሉታዊም ጎኖች ላይ ምላሽ ሰጠተዋል። እስከ ቅርብ ግዜ ብቸኛው የመረጃ አቅራቢ የነበረው የመደበኛው ሚድያም ተደራሽነቱንናየመረጃ ምንጮቹን ለማስፋት ማህበራዊ ሚድያዎች ጋር ደጅ ለመጥናት እየተገደደ ይገኛል ነገር ግን በኢትዮጵያውያን የማህበራዊ ሚድያ አጠቃቀም ላይ በቂ ጥናቶች አለመኖራቸው፣ የዲጅታል ዕውቀት ላይ ያለው ውስንነት እንዲሁም የኢትዮጵያ የማህበራዊ ሚድያ ተጠቃሚውን የሚከላከል የዴታ ደህንነትን የተመለከተ ህግ በተለይም በ2013 ዓ.ም መራጩ ማህበረሰብ ካልተረጋገጡ መረጃዎች እና ከሃሰተኛ መረጃዎች እንዲሁም ካልተገባ የዴታ /ጥሬመረጃ/ አጠቃቀም የሚጠብቁ ህጎች አለመኖር በማህበራዊ ሚድያው የተጋረጠውን አደጋ አስፈሪ ያደርገዋል።
ማስታወሻ – ከላይ የቀረበው በብርሃን ታዬ የተፃፈውን መረጃ በተመለከተ አስተያየታችሁን ብትሰጡን በደስታ እንቀበላለን፡፡