አክሱማይት አብርሃ ተወልዳ ያደገችው፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷንም የተማረችው በጎንደር ከተማ ነው።

እርሷ እንደምትለው በተማረችበት የካቶሊክ ትምህርት ቤት አቅራቢያ የሚገኘው ቀይ አምባ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እርጅና ተጭኖት፣ እንክብካቤ ርቆት ከመማሪያ ክፍል ጎዳና ሊወጣ ቀርቶት ነበር።

በዚህ ትምህርት ቤት ባትማርም፣ የልጅነት ጓደኞቿ፣ የሰፈሯ ልጆች እንዲሁም አብሮ አደጎቿ ተምረውበታል። እርሷ ወደ ተማረችበት የካቶሊክ ትምህርት ቤት ስታመራ አብረዋት የሚሄዱ ጓደኞቿ እዚህ ትምህርት ቤት ነው እውቀት የገበዩት።

የእርሷ ጓደኞች የቀለም ዘር የለዩበት፣ በእውቀት የታነፁበትና ማንነታቸውን የቀረፁበት ይህ ትምህርት ቤት በዘንድሮ የትምህርት ዓመትም ከስድስት መቶ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ያስተናግዳል።

ለአክሱማይት የልጅነት ትዝታ፣ የትውልድ ከተማዋ ማስታወሻ ከሆኑት መካከል ይህ ትምህርት ቤት አንዱ ነው።

ቀይ አምባ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ የሚያስተምር ሲሆን፣ አክሱማይት እንዲህ ለእርጅናና ለጉስቁሉና እጁን ሰጥቶ ያየችው ድንገት ወደ ከተማው ባቀናችበት አጋጣሚ ነው።

ትምህርት ቤቱ የነበረበትን ጉድለት ማየትና መስማት ብቻ ለእርሷ በቂ አልነበረም፤ የኖረችበት ማህበረሰብ ልጆቹን የሚያስተምርበት ትምህረት ቤትን በምን መልኩ ማገዝ እችላለሁ የሚለው የዘወትር ሃሳቧ እንደነበር ታስታውሳለች።

ኑሮዋን በአዲስ አበባ ያደረገችውና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ላይ የተሰማራችው መሃንዲሷ አክሱማይት ትምህርት ቤቱ እንዲህ ጎስቁሎ ስታየው አምስት መቶ ተማሪዎችን ተቀብሎ በእውቀትና በሥነ ምግባር ለማነጽ ይታትር ነበር።

“ክፍሎቹ ፈራርሰዋል፣ ውስጣቸው ጨለማ ነው፣ ወደ መማሪያ ክፍሉ ውስጥ እንስሶች ይገቡ ነበር” ስትል የነበረውን ሁኔታ ታስታውሳለች።

ትምህርት ቤቱ ጥሩ ምድረ ግቢ ቢኖረውም፣ ቅጥሩም አጥሩም ሰፊ ቢሆን፣ ነገር ግን ለተማሪዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መስሪያ የሚያገለግሉ ሜዳዎች የሉትም። ይህንን እንደ ቅንጦት ተቆጥሮ ቢታለፍ እንኳ የመማሪያ ክፍሎቹ በቂ አይደሉም ትላለች አክሱማይት።

በክፍሎቹ ውስጥ የተማሪዎች መቀመጫ ወንበር ማግኘት ከባድ ነበር። ግን ድንጋይ ላይ አስቀምጠው የሚማሩ ተማሪዎች የሚታይበት መሆኑንም ታስተውላለች።

የትምህርት ቤቱን ችግር ያዩ አይኖች ምን አደረጉ?

ቀይ አምባ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የቀለም እድሳት ቢደረግለት ነገ ተመልሶ ቀለሙ ሊፋፋቅ፣ ከጭቃና ከእንጨት የቆሙ ግድግዳዎች ሊፈርሱ እንደሚችሉ መረዳቷን አክሱማይት ትናገራለች። ከዚያ ይልቅ የተሻለ እድሳት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አመነች።

“የተሻለ” ማለት ትላላች አክሱማይት፣ በብሎኬት በጥሩ ሁኔታ ክፍሎቹ ቢገነቡ የሚል ነው።

ይህንን ሃሳብ በመነሻነት ስታስብ ወዳጆቿን፣ ቤተሰቦቿን እና የአካባቢውን ማህበረሰቦች ብቻ ተማምና መሆኑን ከቢቢሲ ጋር ቆይታ በነበራት ወቅት ተናግራለች።

“የእድሳት ሃሳቡን እኔ ባመጣውም የተማመንኩት ግን በማህበረሰቡ እና በወዳጆቼ ነበር” በማለትም የእንቅስቃሴውን ጅማሬ ታስረዳለች።

ማህበረሰቡ በገንዘብና በቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ እንዲሳተፍም በማድረግ በኩል እንደተሳካላት ትናገራለች።

እነዚህ አካላት በገንዘብ ስምንት የመማሪያ ክፍሎችን ለማስራት ወደ 1.6 ሚሊየን ብር ማዋጣታቸውን ትናገራለች።

ትምህርት ቢሮ የክፍሎቹን ጣሪያ በመግዛት መሳተፉንም ታስታውሳለች።

ገንዘብ የማሰባሰብ ስራ በፌስቡክ

ገንዘብ የማሰባሰብ ስራው በአንድ ጀንበር የተሰራ አለመሆኑን የምትናገረው አክሱማይት አብርሃ፣ እርሷና ጓደኞቿ ትምህርት ቤቱን እንደ አዲስ ለመገንባት ካሰቡ በኋላ ከመሰረት ማውጣት ጀምሮ እስከ ጣሪያ ማልበስ ድረስ ያለውን የግንባታ ሂደት ለማከናወን በሂደት በትንሽ በትንሹ ገንዘብ የማሰባሰብ ስራዎችን በፌስቡክ ለማካሄድ እንቅስቃሴ ጀመሩ።

ሰዎች በፌስቡክ የትምህርት ቤቱን የግንባታ ሂደት አይተው ለዚህ ተብሎ በተከፈተው የባንክ ሂሳብ ገንዘብ ከላኩ በኋላም፣ ገንዘባቸው ምን ላይ እንደዋለ ማየት እንዲችሉ በየጊዜው መረጃዎችን የማቅረብ ስራ መስራት ያስፈልግ እንደነበር ታስታውሳለች።

ይህ ሰዎች በስራው ላይ እምነት እንዲኖራቸው፣ እንዲሁም ደግሞ ለሌላ መዋጮ እንደሚያበረታታቸው ትናግራለች።

በፌስቡክ መረጃ የሚለዋወጠውና በመዋጮ የሚሳተፈው ግለሰብ ከራሱ ባለፈ ሌሎች ወዳጆቹ፣ የማህበራዊ ሚዲያ አጋሮቹ እንዲሳተፉ በመቀስቀስ ረገድ የራሱን አስተዋጽኦ ማድረጉንም ትገልጻለች።

ወደ አሜሪካም ለግል ጉዳይዋ በተንቀሳቀሰችበት ወቅት የጎ ፈንድ ሚ አካውንት በመክፈትም በአጠቃላይ ከ13 ሰዎች 17000 ዶላር አካባቢ መሰብሰቡን ትናገራለች።

ከአገር ውስጥ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች በርካታ ሰዎች ገንዘብ በማዋጣት መሳተፋቸውን፣ እርሷም በየጊዜው የሂሳብ ሪፖርት በማቅረብ ለተሳታፊዎች ገንዘባቸው ምን ላይ፣ ለምን ጥቅም እንደዋለ በማሳየት በሃላፊነት ስሜት መስራቷን ታስረዳለች።

ትምህርት ቤቱ የተገነባው በሁለት ዙር ነው የምትለው አክሱማይት፣ የመጀመሪያውን አራት ክፍሎች የያዘውን ብሎክ ለመገንባት ሰባት ወር መፍጀቱን ትናገራለች።

ይህንን ግንባታ በ2012 መስከረም ወር ላይ አጠናቅቃ ማስረከቧን በማስታወስ አክላም ክፍሎቹ ሲገነቡ ጎን ለጎን የገንዘብ መዋጮው እየተካሄደ ሁለተኛው አራት ክፍል የያዘው ብሎክ ግንባታው ተጠናቅቆ በቅርቡ እንደምታስረክብ ገልፃለች።

ትምህርት ቢሮ ለአራት ክፍሎች የተማሪዎች መቀመጫ በመማቅረብ ተሳትፎ ማድረጉንም ትናገራለች።

ፌስቡክን ለበጎ ማህበራዊ ግልጋሎት

የፌስቡክ ዓለም ተሳታፊው ብዙ ነው። ከፖለቲካው እስከ እዚህ ግባ የማይባሉ ቧልቶች ይዘወተሩበታል። ሁሉም ልቡ ወደፈቀደው መንደር ጎራ ብሎ በመከተል ይሳተፋል።

አክሱማይት ከፌስቡክ የተማርኩት ሁላችንም ተመሳሳይ የሆነ ፍላጎት እንደሌለንና እንዲህ አይነት በጎ መነሳሳቶችንም ለማገዝ ደግሞ ልብ እና የማይሰስት እጅ ያላቸው ሰዎች መኖራቸውን ነው ትላለች።

ተሰርቶ የሚያዩ ከሆነ እና ገንዘባቸው ተገቢው ስፍራ ላይ መዋሉን ካወቁ በርካታ ሰዎች ለውጥ ለሚያመጣ ነገር ለመተባበር እንደሚሹ ትመሰክራለች።

ከዚህ በመቀጠል በፋሲል ክፍለ ከተማ ቀበሌ13 የንባብ ማዕከል ለመገንባት በእንቅስቃሴ ላይ መሆኗን ገልጻ፣ ዘንድሮ ይህንን ካሳካሁ የሚቀጥለው ዓመት ደግሞ ሌላ እድሳት የሚያስፈልገው ብዙዎችን በእውቀትና በሥነ ምግባር የሚያንጽ ትምህርት ለማደስ እቅዶች አሉኝ ብላናለች።

ቀይ አምባ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በዚህ አመት 670 ተማሪዎችን ተቀብሎ በፈረቃ ለማስተማር ተሰናድቷል።

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *