በአገራችን በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ምክንያቶች የንፁህ ዜጎች ሕይወት በአሰቃቂ (በአሳዛኝ) ሁኔታ እያለፈ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በእነዚህ አሳዛኝ ጥቃቶች በርካቶች ህይወታቸው አልፎ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ከቤት ከቄያቸው ተፈናቅለው፤ ሌሎች በርካቶችም ለከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ እንዲህ ያለውን አሳዛኝ ክስተት ለመግታት ደግሞ ሁሉም ወገን የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል፡፡ በተለይ ደግሞ ወጣቱ አንድም ግጭቶች ከመቀስቀሳቸው በፊት በመከላከሉ ረገድ በሌላም በኩል ግጭቶች ከተከሰቱ በኋላም ግጭቶችን ለማብረድ የላቀ ሚና ያለው መሆኑ ይታወቃል፡፡ እኛም በዚህ ረገድ የተለያዩ በሠላም ላይ ያተኮሩ የሬዲዮ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት ማሕበራዊ ሚዲያን ለጥል እና ለመለያት ሳይሆን ለመቀራረብ እና ለአንድነት የሚውልበትን መንገድ በማመቻቸት የድርሻችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል፡፡ በመሆኑም በዚህ ድረገፅ ላይ የሚገኙት ማናቸውም መረጃዎችም መነሻ እና መድረሻቸውን ሠላምን ያደረጉ ናቸው፡፡
በአገራችን ዘላቂ ሰላም ማስፈን የሚቻለው ሁላችንም የድርሻችንን መወጣት ስንችል ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም በሰላም ተከባብሮ በመኖር፣ የዜግነት ግዴታን ስለመወጣት፣ በበጎ ፍቃደኝነት አገልግሎት ስለመሳተፍ እና መሰል ማናቸውም ተመሳሳይ በጎ ነገሮች የተመለከቱን ሐሳቦች ታደርሱን ዘንድ እየጠየቅን በፌስቡክ፣ በቴሌግራምም ሆነ በዩቲዩብ ቻናላችን ቤተሰብ ትሆኑን ዘንድ በዚሁ አጋጣሚ እንጋብዛለን፡፡
የፕሮግራማችን ዓላማዎች
- ወጣቱ ከግጭት ርቆ ለሠላም ዘብ እንዲቆም ማብቃት እና ማሳወቅ
- ሐሰተኛ የማህበራዊ መረጃን በማጋለጥ ጤናማ ማሕበራዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ መልዕክቶችን በስፋት ማስተጋባት
- ወጣቶች በሚማሩበት ከፍተኛ ተቋም ሆነ በአካባያቸው ለለውጥ የቆሙ ‘‘የሠላም አምባሳር’’ እንጂ የማንም ወገን መጠቀሚያ እንዳይሆኑ ማንቃት
- የዳበረ ሰላማዊ ባህልን፣ እሴቶችን በስፋት በማሕበረሰቡ ውስጥ ማስረፅ
- በአገራችን ግጭትን ለመከላከል የሚያግዙ የተለያዩ አይነት ጠቃሚ ልምዶችን በራዲዮ ሆነ በማሕበራዊ ሚዲያ ማቅረብ
- ለዲሞክራሲ እሴቶች መዳበርና ለሠላም ለእርቅና መቻቻል የሚያግዙ ተከታታይ ፕሮግራሞችን ማቅረብ
- መቻቻልን የሚያጎለብቱ፣ በተለያዩ ኃይማኖት የዕምነት አባቶች እና የተለያዩ ብሔሮች የአገር ሽማግሌዎች መካከል ዘላቂ የሆነ ሠላም እንዲፈጠር ተከታታይ የውይይት መድረክን ማዘጋጀት
- ዜጎች በማህበራዊ ሚዲያ ሲጠቀሙ ያገኘኙትን መረጃ ትክክለኛነት እንዲያጣሩ፣ የሐሰት መረጃን በቸልተኝነት ከማጋራት (ሼር ከማድረግ) እንዲቆጠቡ ማሳወቅ
- ሁሉን አቀፍ (አካታች) ውይይት እና ተከታታይ መረጃዎችን በቅርብ የግጭት መከላከል ሥራዎችን በስፋት ማቅረብ
- በኃይማኖት፣በብሔርና በፖለቲካ አመለካከት የተለያዩ ሰዎችን በአንድ መድረክ በማገናኘት የመለያየት ሳይሆን የመቀራረቢያ የሐሳብ ድልድዮችን በማኖር ጥላቻንና የተካረረ ልዩነትን ማርገብ
- ማሕበራዊ ሚዲያን ለሠላም እና እውነተኛ መረጃን ለማሰራጨት ብቻ ለማዋል የሚተጉ አድማጮችን ቁጥር ማሳደግ፤
- ለሠላም ዋጋ በመስጠት ወጣቱ ለከተማው ሆነ ለሐገራችን ሠላም የድርሻውን እንዲወጣ ማብቃት
ራዕይ
ሠላምን የሚያስጠብቁ፤ በብሔር፤ በቋንቋ ሆነ በፖለቲካ አመለካከት ለማይመስሉት ወገኖች ዘብ የሚቆም እና የዜግነት ግዴታውን በየእርከኑ ከመወጣት ወደ ኋላ የማይል ትውልድ ተፈጥሮ ማየት
ተልዕኮ
የዚህ ፕሮጀክት አጠቃላይ ተልዕኮ በሐገራችን በየጊዜው የሚከሰቱ ግጭቶችን ለማስቆም የድርሻቸውን መወጣት የሚቻላቸውን ወጣቶች በእውቀት ማበልፀግ እና ለፀብና ቁርሾ የሚውሉ አላስፈላጊ ትርክቶችን በብስለት መመከት የሚችሉን ዜጎች ቁጥር በራዲዮ ፕሮግራም፣ በማሕበራዊ ሚዲያ እና በሌሎችም የመልቲሚዲያ ውጤቶች አማካኝነት ማብዛትና የሚሹትን ጠቃሚ መረጃ ማቀበል ነው፡፡